ይድረስ ለወ/ት ብርቱካንና መሰል የወያኔ እሥር ቤት ሰለባዎች -ይሄይስ አእምሮ

ፍኖተ ነፃነት
By ፍኖተ ነፃነት July 29, 2012 12:07

ይሄይስ አእምሮ

እንደመነሻ ያህል

ለመሪያችን ለአቶ መለስ ዜናዊ የተሟላ ጤንነትን እመኛለሁ፡፡ ‹እንደ እናቴ ሳይሆን እንደሚስቴ አውለኝ› እንደሚባለው እንደሟርተኞቹ የተቃዋሚ ልሣናትና የግል ሚዲያዎች ሳይሆን እንደ በረከት ስምዖንና ሽመልስ ከማል ምኞት ያድርግልን፡፡ የአቶ መለስ ጤንነት ከሁሉም በላይ ነው፡፡ እርሳቸው አንዳች ነገር ቢገጥማቸው ከፕሬዝደንታችን ከአቶ መቶ አለቃ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ እምብዝም በማይተናነስ ሁኔታ ሀገራችን ትልቅ የሀገር ምሰሶ ታጣለችና መሪያችን በተሎ አገግመው ወደ መደበኛ ሥራቸው ይመለሱ ዘንድ እንጸልይላቸው፡፡ ይህች ደህና ሰው የማይወጣባት ሀገራችን ለከፋ ሀዘን እንዳትዳረግ እግዜር አደራውን፡፡ የሚወራበትን የጠላትና የኢሳት ቲቪ ወሬ ሁሉ ህልም እልም ያድርግልን፡፡

ወደዚህ ጽሑፍ ከማምራቴ በፊት በዘሐበሻ ድረ ገፅ ላይ በሄኖክ ዓለማየሁ ስለብርቱካን ሚደቅሳ የቀረበ አንድ ዘገባ አነበብኩ፡፡ በዚያ ተመሳሳይ ጉዳይ ላይ አንዳች ነገር ልጽፍ ከወደድኩ ብዙ ጊዜ ሆኖኛል፡፡ ምክንያቱም የአምባገነኖችን ባሕርይ በተለይም የወያኔን ልከስክስ ጠባይ ጠንቅቄ ስለማውቅ እሥረኞችን እንዴት አፍ እንደሚያዘጋ ያለኝን ግምት ለመግለፅ እመኝ ነበርና፡፡ አሁን ዕድሜ ለዘሐበሻ ተሳካልኝ መሰለኝ፡፤ ይህችን ማስታወሻ ለዚሁ ድረ ገፅ የሚሰጥልኝ ሰው ባገኝ ዕድለኛ ነኝ፡፡ የነሱ አድራሻ የለኝም፡፡ በቴክሎጂ ባላገር ስለሆንኩ እንዴትና የት እንደማገኘውም አላውቅም፡፡ ያሉኝንም አድራሻዎች በስንት መከራ ነው ያገኘሁት፡፡

መግቢያ

አንድ ወቅት አንድ ሽማግሌ የሀገር መሪ ወደ አንድ ሌላ ሀገር ለጉብኝት ይሄዳሉ፡፡ የሄዱት ባለቤታቸውን ሳያስከትሉ ነው፡፡ የሄዱበት ሀገር በሥልጣኔ ከእርሳቸው ሀገር በእጅጉ የላቀ ነበር፡፡ በደንብ ተከታተሉኝ አደራ፡፡ የዚያ ሀገር የስለላ መረብ ለዚህ ሽማግሌ የሀገር መሪ ለመኝታ ሰዓታቸው አንድ ነገር አቀነባብሮ ያዘጋጅላቸዋል፤ ብዙዎቻችን የምንወደውን – ከወጥመዱ ለመውጣትም ብዙዎቻችን የሚያቅተንን ነገር፡፡ ያ ነገር ወሲብ ነው፡፡ ልብ በሉ፡፡ ሰውዬው የቀረበላቸው ግብዣ ያንጀት መስሏቸው አዲስ ነገር በአዲስ ጉልበትና በአዲስ ወኔ ሲኮመኩሙ አደሩ፡፡ ሴትዮዋም ሥልጡን ነበረችና እንደጉድ ስታርገበግባቸው አድራለች – ሲደረግ የማይታፈርን ነገር ስናወራ አንፈር ግዴለም፡፡ ትኩረታችንን ግን ከመነሻችን እንዳናዛውር ልብ እንበል፡፡ በማግሥቱ  ዱብ ዕዳ ገጠማቸው፡፡ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት “ውድ ወዳጃችን ፕሬዚደንት እገሌ ሆይ! ዛሬ ሌሊት ያደረጉትን ሁሉ  በፊልም ቀርጸነዋል፡፡ ይህንን የወሲብ ጀብድዎን በተለይ ለሚስትዎና ለልጆችዎ፣ በአጠቃላይ ደግሞ ለሀገርዎ ሕዝብ በቴሌቪዥን መስኮት ሳንለቀው ሀገርዎ እንድታደርግልን የምንፈልገውን እንዲህ እንዲህ ያለ ነገር እንዲያደርጉልን በአክብሮት እንጠይቅዎታለን፤ ባያደርጉ ግን የሚዋረዱት እርስዎ ነዎት!” ይሏቸዋል፡፡ ይሄኔ ብልኁ(ጡ?) ሽማግሌ ቀበል ያደርጉና “ እንዴ! ይሄማ በጣም ግሩም ነው፡፡ እንዲያውም በዚህ ዕድሜየ እንዲህ ያለ ከፍተኛ ጥንካሬንና ብርታትን የሚጠይቅ ሥራ መሥራቴን የሚገልጥ ተግባሬን ለሀገሬ ሕዝብ ካሳያችሁልኝ እኔም ሞቅ ያለ ገንዘብ  እከፍላችኋለሁ፡፡ እባካችሁን አሁኑኑ ልቀቁት፡፡ እኔም እስኪ ልየው፡፡ ከሀገሬ የምትፈልጉትን ግን እስከ ወዲያኛው አታገኙም፡፡” ብለው አዋረዷቸው፡፡ ሰዎቹ ምን ያድርጉ? ኪሣራ፡፡

ሽማግሌው የሀገር መሪ ለተዘረጋባቸው ወጥመድ አልተሸነፉም፡፡ ከእርሳቸው ክብርና ሞገስ ይልቅ የሀገራቸውን ሉዓላዊነትና ኅልውና አስቀደሙ፡፡ የግል ሕይወት አላፊ ጠፊ ነው፡፡ የሀገር ኑባሬ ግን ዘላለማዊ ነው፡፡ እናም አልተንበረከኩም፡፡ ትልቁን ዓላማቸውን በትንሽ ወጥመድ አልለወጡም፡፡

ይህ ዓይነቱ ነገር በስለላው ዓለም አካባቢ ‘blackmailing’ በመባል ይታወቃል፡፡ ይህ ዓይነቱ ወጥመድ ግን በተለይ በአጥማጁ በኩል ከፍተኛ ጥንቃቄን ይጠይቃል፡፡ ማን ለየትኛው ወጥመድ ይበልጥ ስስ ነው ብሎ አስቀድሞ ማሰብን ያጠይቃል፡፡ እንደሽማግሌው ያለ እምነተ ጠንካራ ሊያጋጥም ስለሚችል ወጥመዱ ሁሉ ላይሠራ እንደሚችል መገመት ተገቢ ነው – እንደ ደህንነት ሠራተኛ መጠን፡፡ ወያኔ ደግሞ በዚህ ጉዳይ ታላቅ ኤክስፐርት ነው፡፡ ብዙዎችን ድራሻቸውን ያጠፋበት ዘዴ ይሄው ሥልት ነው፡፡ እንኳንስ እሥር ቤት የከተታቸውን ምሥኪን ዜጎች ይቅርና ድፍን ባለሥልጣናቱን ሳይቀር በዚህ ዕኩይ ሥልት ነው ጠፍንጎ የያዛቸው(‹ስኳር› በማቅመስ፣ ወንጀል እንዲሠሩ ሁኔታዎችን በማመቻቸትና ያንንም ለክፉ ቀን እንዲሆነው  መዝግቦ በማስፈራሪያ ካርድነት በመያዝ በሰው ላይ መጫወቱን ወያኔ የተካነበት ሙያው ነው…)፡፡ ይህ ካርድ የሚባለው ነገር መጥፎ ነገር ነው፡፡ የኅሊናን ጤናማነት አስወግዶ ራስን ያስረሳል፤ በጥቅምና በይሉኝታ ያሳውራል፤ በጥፋተኝነት ስሜት ሸብቦ የዘላለም ባሪያ ያደርጋል፡፡ ከጥራዝ ነጠቃዊ ትንተና አንጻር በዚህ ጉዳይ ከበርካታ ምሳሌዎች ጋር ብዙ መናገር ብችል ደስ ባለኝ፡፡ ግን ጊዜ የለንም፡፡ ይህ ዓይነቱ ዘዴ በተለይ እንደወያኔ ያለው ቅሌታምና ምንም ዓይነት ሃይማኖታዊም ሆነ ሞራላዊ ሰበዝ የሌለው ስድና ባለጌ የወሮበሎች መንጋ ውስጥ ገብቶ በተግባር ሲታይ ላይደረግ የማይችል የብላክሜይል ዓይነት እንደማይኖር መገመት አይከብድም፡፡ በዚህ ጊዜ አያድርስ ከማለት ውጪ ሌላ የምንለው የለም፡፡ እንደሽማግሌው የሀገር መሪ ያሉ ጎበዞች በዚያ ሂደት የተገኙት ወድደው ሳይሆን ተገድደው መሆኑን ይረዱና ከዚያ ሁኔታ ውስጥ ሲወጡ አፍንጫህን ላስ ብለው የኅሊናቸውን ጎዳና ሊከተሉ ይችላሉ፡፡ እንደ ኦብኮዋ አልማዝ ሠይፉ ያሉ ደካሞች ደግሞ እንደተሸነፉ በዚያው ይጠፋሉ፡፡ ወያኔ በእሥር ቤት ውስጥ በተለይ በሴቶቹ ላይ ምን ሊያደርግ እንደሚችል ከሰይጣን በስተቀር ማንም ሊያውቅ አይችልም፡፡ ወያኔ ማለት ከሰይጣንም በላይ ነው፡፡ ኤች አይ ቪ ያለባቸውን ሰዎች ከትግራይ እያሰባሰበ መላዋን ኢትዮጵያ እንዲበክሉ ወደየክልሉ የሚያሰራጭ፣ ኢትዮጵያን ወዳድ ትግራውያን አዛውንትን በወባ መከላከያ ክኒን መልክ በተዘጋጀ መርዘኛ ክኒን የሚፈጅ፣ ‹ከእናንተ በመፈጠራችን እንኮራለን› እያለ በሕዝብ መካከል የልዩነት ዘር የሚዘራ ዘረኛ ቡድን … ሰይጣን እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡ ‹ሰይጣንን የፈጠረው ማን ነው?› ተብሎ ቢጠየቅ እንደኔ የምመልሰው ‹ወያኔ ነው› ብዬ ነው፡፡ እጅግ ተንኮለኞች፣ እጅግ ሸረኞች፣ እጅግ ጋጠ ወጦች፣ እጅግ የሁሉም መጥፎ ነገሮች ማምረቻዎችና መጋዘኖች ናቸው፡፡ ስለዚህ በአንደርባቸው ውስጥ ያስገቧቸውን ማምለጫ ያጡ ዜጎች አንገት ቢያስደፉ፣ መንገድ ቢያስለውጡ፣ ቃል ቢያሳጥፉ፣ አደራ ቢያስበሉ… በተንሸናፊ ወገኖች ብዙም አልፈርድም፤ ወያኔዎችን በደንብ አውቃቸዋለሁና፡፡ ወያኔዎች የሰውነት ባሕርይ ቢኖራቸው ነበረ ሰብኣዊነትን ሊያከብሩ ይችሉ የነበሩት፡፡ እነሱ ለራሳቸው ያንድኛውን ሚስት/ባል እየቀሙ – በመገዳደልም ጭምር – የሚያገቡ፣ አንዳቸው ባንዳቸው ሚስት የሚወልዱ፣ ከኢአማኒነት(Atheism) እና ከሴተኒዝም(Satanism) ውጪ አንዳችም ኮንቬንሽናል የሚባል ሃይማኖት የሌላቸው፣ የሀገር ፍቅርና ብሔራዊ ስሜት የሚባል ያልፈጠረባቸው ሆድ አምላኪዎች፣ ከሥልጣንና ጥቅም በስተቀር ሕዝባችንና ሀገራችን የሚሏቸው ኅላዌያት የሌሏቸው፣ ከመጥፎ የአራዊት ዝርያ የሚለያቸው በሰው አምሳል የሚንቀሳቀሱ መሆናቸው … በደምሳሳው የለየላቸው ዋልጌዎችና ከሁሉም ማኅበረሰብዓዊ ክሮች የወጡ በመሆናቸው ባጭሩ የተዋጣላቸው ሰብዓ ሶዶም ወገሞራ ናቸው፡፡

ስለዚህ … ስለዚህ ብዬ ምን ልበል? ብቻ… ስለዚህ በወያኔ እሥር ቤት ፈግቶ የሚወጣን ሰው አእምሮ ማስተካከል የሚችልና ወደነበረበት የቀደመ ይዘት የሚለውጥ በልምድና በትምህርት የበሰለ የሥነ አእምሮና የሥነ ልቦና ጠቢብ ያስፈልገናል፡፡ እንዲህ ያለ ባለሙያ ሰው በወያኔም ሆነ በተመሳሳይ ሌላ አውሬ በአካልም ሆነ በመንፈስ ተጎሳቁሎ የሚወጣ ዜጋችንን በምክርና በህክምና እንደገና አንፆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ያደርግልናል፡፡ ሀገራችንን ሰው እስኪመራት ድረስ ብዙ የምንከፍለው ዕዳ አለ፡፡ ከሁሉም በላይ ግን በወያኔዎች የምንገፈግፈው ሃይማኖታዊና ሞራላዊ የዕዳ ውዝፍ እስከመቼውም ተከፍሎ የሚያልቅ አይመስለኝም፡፡ ‹ይህን ብታደርጊ/ብታደርግ እንገድልሻለን/እንገድልሃልን› ከሚለው ተራ ማስፈራሪያ የበለጠ  በረቀቀ የቴክኖሎጂ ቀረጻ ዜጎቻችንን አፋቸውን የሚያዘጋ ልዩ ዕኩይ ድርጊት በዱርዬዎችም ሆነ በነሱ በወያኔዎቹ በራሳቸው ሊፈጽሙባቸው ይችላሉ እያልኩ ነው፡፡ እንደተግባባን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ዋናው ሰኞን አለመሆን ነው፡፡ በዬሽርንቁላው ተሸጉጦ የሚጫጭር የኔ ቢጤውማ ምን ያገኘዋል፡፡ ግን እንዳይፈረድብን አንፍረድ፡፡ አንድ ሰው የቻለውን ያደርጋል፡፡ በዚህ ወይም በዚያ ምክንያት ሲደክመው ግን ከትግሉ ሜዳም ሆነ ከአጠቃላይ ማኅበራዊ ግንኙነቱ  ሊያፈገፍግ ይችላል፡፡ ያኔ የአሁኑን ሳይሆን የጥንቱን ማየት ይገባናል እንጂ የቀድሞ ባለውለታዎቻችንን ቤተስኪያን እንደገባች ውሻ ችው ችው ማለት አግባብ አይደለም፡፡ ‹የዱሮ ጓደኛህን በምን ቀበርከው› ቢሉ ‹በሻሽ› ‹የኋለኛው እንዳይሸሽ› እንደተባለው እንዳይሆን በፈተና ስናልፍ ልዩ የሞራልም ሆነ የማቴርያል ድጋፍና ማበረታቻ እንደሚሰነዘርልን ሁሉ በፈተና ጥሩ ውጤት ሳናመጣ ስንቀር ደግሞ ቅስም የሚሰብር ትችት ከመሰንዘር በመቆጠብ ፈተናውን እንዴት ማለፍ እንደሚገባን ብንመከር ይበልጥ አወንታዊ ነው፡፡  እንደአልባሌ ሰዎች የፊተኛውን በመርሳት የአሁኑ ላይ ብቻ አተኩሮ አጥንት ሰርስሮ በሚገባ የትችትና የዘለፋ ናዳ መወራረፍ ማንንም አይጠቅምም፡፡ ማረፍ የሚፈልግ ይረፍ፡፡ ይህን የምለው እንደ አጠቃላይ እንጂ አሁን ማንንም በአእምሮየ አስቤ አይደለም፡፡

በመሠረቱ ትግል ወንዝ ነው፡፡ ታጋይ ውኃ ነው – የኔ ትንተና ነው፡፡ ወንዙ ሁልጊዜ አለ፤ ውኃው ግን በየሴከንዱ ይቀያየራል፡፡ የኛ ችግር እንደሚመስለኝ ወንዙም ውኃውም ሳይቀየሩ ዝንታለማቸውን አብረው ይኑሩ ከሚል የሚመነጭ ነው፡፡ ወንዙ እስካለ ድረስ ውኃው እየተቀየረ ወደምንፈልገው ደረጃ ለመድረስ መጣር ይኖርብናል፡፡ ደግሞም በተቻለን ፍጥነት ከ ‘personality cult’ መውጣት ይኖርብናል፡፡ የወያኔዎች የአሁኑ ድንጋጤና ብዥታ ከዚህ ይነሳል፡፡ መለስን እንደ አምላክ ሲያዩና እንደጣዖትም ሲያመልኩ ኖረው አሁን  ፈጣሪ ድንገት ይህ ሰው አምላክ አለመሆኑን ሊያሳያቸው ዳር ዳር ሲል የሚይይዙትንና የሚለቁትን አጡ፤ ከእናታቸው ጉያ እንደወጡ ጫጩቶችም ሆኑ፡፡ ራሳቸውን በሚያስችል ሥርዓት ውስጥ ስላልነበሩና በአንድ ሰው ሳምባና ልብ ይኖሩ ስለነበር ዙሪያ ገባው ገደል ሆነባቸው፡፡ በዚያም ምክንያት መለስ ገና በጣር ላይ እያለ አንዱ በባሌ ሌላው በቦሌ ለመፈርጠጥ አቆበቆቡ፡፡ የግለሰብ አምልኮት ባይኖር ኖሮ ‹ከሣር ቤት አንዲት ሣር ብትነቀል ቤቱ አያፈስስም› የሚባለውን ብሂል ለይምሰል ሳይሆን ከምር ሊያቀነቅኑ በተቻላቸውና በተገባቸውም ነበር፡፡ ስለዚህ ከግለሰብ አምላኪነት አሁኑኑ ወጥተን ማንም ቢንሸራተት በሚደነገገው ሕግ መሠረት መሥፈርቱን የሚያሟላ ማንም ሰው ሊተካበት የሚችል ሥርዓት እንዘርጋ፡፡ ግለሰብን ያመነ ጉም የዘገነ እንበል፡፡

የወያኔን ሸርና ተንኮል በተለይ በታሣሪ ወገኖቻችን ላይ የሚፈጽመውን ታሪክ ይቅር አይለውም፤ በቅርቡ እንጠብቅ፤ ቁናው ተሠፍቶ አልቋል – የየመክሊታቸውን ያገኛሉ፡፡ ደርግ እንኳን እንደወያኔ በታሣሪዎች ላይ አልጨከነም፡፡ መግደል ጥሩ ነው፤ በአግባቡ ማሰቃየትም ጥሩ ነው – ደርግ ያን አድርጓል፤ ሩህሩህ ጨካኝ ነበርና፡፡ ነገር ግን በሚዘገንን መልክ ሥነ ልቦናን በማይሽር ጠባሳ እስከወዲያኛው ሰቅዞ መያዝ ከወንጀሎችና ከኃጢያቶች ሁሉ የከፋ ነው፤ ይህ ደግሞ የወያኔ ተፈጥሮ ነው – ወያኔ የጨካኝ ጨካኝ ነውና፡፡ ደርግ ገዳይ ነበር – ሥጋን ገዳይ፡፡ ወያኔ ግን ሥጋን ብቻ ሳይሆን መንፈስንም ይገድላል፡፡ ለዚህ ነው ብዙ ታሳሪዎች ሥጋቸው እንኳን ሳይሞት በመንፈስ እየሞቱ ከትግልና ከማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች በራሳቸው ፈቃድ ወይም በተጣለባቸው ገደብ ምክንያት የሚገለሉት፡፡ ታምራት ላይኔን አስቡ፡፡ ሌሎችንም አስቡ፡፡ በመንፈስ እንዳያንሰራሩ አድርጎ ገድሎ ስለሚለቃቸው ከእሥር ከወጡ በኋላም እሥር ቤት እንዳሉ ያህል እንዲሰማቸው ይገደዳሉ፡፡ የትግል ወኔን ማኮላሸትና የመኖር ተስፋን ማጨለም የወያኔዎች ትልቁ ችሎታ ነው፤ እናም በወያኔ ሰለባዎች አንፍረድ፡፡ እነሱ የሚሰማቸው እንዲሰማን ቢያስፈልግ እነሱ ያለፉበትን ውጣ ውረድ መቅመስ ይኖርብናል፡፡ ለተቀማጭ ሰማይ ቅርብ ነው፡፡ አሁን አሁን ለነሰሎሞን ተካልኝና ለነንዋይ ደበበ ሳይቀር ማዘን ይዣለሁ፡፡ የገቡበትን የኅሊና ቀውስና መንስኤ ሳናጤን በጅምላ ፍርድ መኮነን እንደማይገባን እየተሰማኝ መጥቻለሁ፡፡ አእምሮ እጅግ ስስ (sensitive) ነው፡፡ በቀላል ይበላሻል፤ በቀላልም ወደ መልካም ነገር ያቀናል፡፡ ክፉ ሰው በምክንያት ደህና ይሆናል፤ ደግ ሰው በምክንያት ወይ አለምክንያት ወደክፋት ጎዳና ሊያመራ ይችላል፡፡ ዓለም ዘወርዋራ ናት፡፡ ሕይወትም እንዲህ ናት፡፡ ገና ብዙ እናያለን፤ ዕድሜ ይስጠን እንጂ፡፡

ስለሆነም ብርቱየም በርቺልን፡፡ ደቤም በርታልን፡፡ ሶሎሞንም ወደ ጤናማ ኅሊናህ ተመለስልን፡፡ ንዋይም ወደ ኅሊናህ ምጣልን፡፡ በመልማታችሁ እንጂ በመጥፋታችሁ እኛም ሀገርም አንጠቀምም፡፡ እግዚአብሔር የሚሸሹንን ይመልስልን – ልባቸውንም እንደቀድሞው ያጠንክርልን፡፡ አሳዳጆቻችንን ልብ ይስጥልንና ስሜታችንና ችግራችን እንዲገባቸው ያድርግልን፡፡ አዳዲሶችንም ወደ ትግሉ ማዕከል ያምጣልን፡፡ መለወጥ የሚቻለው ታላቁ እግዚአብሔር ነውና መልካም እረኞችን ያብዛልን፡፡ ጀግኖቻችን ከየተደበቁበት ወጥተው ይህን የመከራ ዘመን ያሻግሩን፡፡ መጠላለፍና መነቋቆር በቅቶን የአንዲት ሀገር ልጆች ነንና በፍቅርና በመተሳሰብ ለመኖር ያብቃን፡፡ መጪው ዘመን ያለ መለስ ብሩኅ ነው! አሜን፡፡

ፍኖተ ነፃነት
By ፍኖተ ነፃነት July 29, 2012 12:07