ዘረኝነት በየትኛውም ዓይነት ቅርጽና ይዘት ቢመጣ ልናወግዘው ይገባል!

ፍኖተ ነፃነት
By ፍኖተ ነፃነት March 28, 2014 10:32

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
UNITY FOR DEMOCRACY AND JUSTICE PARTY(UDJ)

ከአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ!
በታሪካችን የታዩ ጉድለቶች ቢኖሩም፣ በሀገራችን የተለያዩ ብሔረሰቦች በመከባበርና በመፈቃቀር ለረጅም ዓመታት አብሮ እንደኖሩ ይታወቃል፡፡ ይህ የአብሮነት የመኖር መንፈስ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲፈተን ይታያል፡፡ ባላፉት ሃያ ዓመታት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ በመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ በንግዱ ማህበረሰብ፣ በሲቪክ ተቋማት ወዘተ የታዩ አሳሳቢ ጽንፈኛ አመለካከቶች በጊዜ እርምት ሊወሰድባቸው አልተቻለም፡፡ በተለየ የነገ ሀገር ተረካቢ የሆነው ወጣቱ፣ በጽንፈኛ አመለካከቶች መጠመዱ፣ እንደ ሀገር ሊያሳስበን ይገባል፡፡
ፓርቲያቸን በቅርቡ በባህር ዳር የተከሰተውን አሳፋሪ ተግባር በጽኑ ያወግዛል፤ በዚህ አስነዋሪ ተግባር ተጠያቂ የሆኑ አካላትን ለሕግ እንዲያቀርቡ ይጠይቃል፡፡ ስፖርት ለሰላምና ለወዳጅነት መሆኑ ቀርቶ፣ የዘረኝነት ማንፀባረቂያ መሆን የለበትም፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በተለያዩ ወቅት ህገ-ወጥ በሆነ ሁኔታ ከቦታቸው በግፍ እንዲፈናቀሉ የተደረጉ ወገኖች ወደ ቀያቸው ተመልሰው፣ በሀገራቸው ሰርቶ የመኖር መብታቸው እንዲከበር እንጠይቃለን፡፡ በቅርቡ ለአለፉት ሃያ ዓመታት ከኖሩበት ኦሮሚያ ክልል ም/ሸዋ ዞን አምቦ ዳኖ ወረዳ የተፈናቀሉ ወገኖች፣ ዘራቸው እየተቆጠረ በህጋዊነት ከሚኖሩበት አካባቢ የማፈናቀል ተግባር አንድነት በጥብቅ ያወግዛል፡፡ ዜጎችን ላይ እንዲህ ያለ ግፍ የሚፈጽሙ ካድሬዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን፡፡ አንድነት እየጎላ የመጣው አለመተማመንና ውጥረት መባባስ ያለንበት የተበላሸ የፖለቲካ ስርዓት ነጸብራቅ ነው ብሎ ያምናል፡፡
ባለፉት አራት አስርት ዓመታት የብሔረሰቦች የመብት ጥያቄ የሀገራችን ፖለቲካ በሁለት ጽንፎች ወጥሮ ከያዙ ስስ ጉዳዮች አንዱ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በአንዱ ጫፍ ያለው ኃይል የብሔረሰቦችን ህልውና የካደና በሀገራችን ውስጥ ያለውን ብዝሀነት እንደ ስጋት የሚወስድ ነው፡፡ በብሔረሰብ ዙሪያ መደራጀት ጠቃሚ አይደለም ብሎ ማመን አንድ ነገር ሆኖ፣ መብት መሆኑን ግን የማይቀበልና የቆሞ ቀሮች አስተሳሰብ ባለቤቶች ስብስብ ነው፡፡
በሌላው ጫፍ ያለው ኃይል የራሱን ብሔረሰብ መብት ለማስከበር በሚል ስም፣ የሌሎችን እኩልነትን የማይቀበል ነው፡፡ ኢህአዴግና መሰሎቹ የብሔረሰቦችን የመብት ጥያቄ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ በቅጡ ሳይረዱ፣ ከውጭ በተቀዳ ርዕዮት ዓለም ለመተንተን የተሞከረበት አሳዛኝ የታሪክ ሂደት ለማለፍ ተገደናል፡፡ ይህ ኃይል ራሱን ከጥላቻና ከታሪክ እስረኝነት ነጻ ያላወጣና የብሔረሰብን መብት ያለቅጥ በመለጠጥ የሀገርን አንድነትና ሉዓላዊነት አደጋ ላይ ጥሎቷል፡፡
እንድነት ፓርቲ በብሔረሰብ መብት ዙሪያ በሁለቱም ጫፍ ላይ ያሉ አስተሳሰቦች ወደ መሃል መምጣት አለባቸው ብሎ ያምናል፡፡ የአንዱን ስጋት ሌላኛው ቦታ ሊሰጠው ይገባል፡፡ የዚህ ትውልድ አንዱና ዋንኛ ቁልፍ ተልዕኮ ይህን ማሳካት ነው ብለን እናምናለን፡፡
ፓርቲያችን በሀገራዊ አጀንዳዎች ዙሪያ ተሰባስቦ ትግሉን መምራት ትክክለኛው የትግል መስመር ነው ብለን እናምናለን፡፡ የግለሰቦች መብት ሳይከበር፣ የቡድን መብት ሊከበር እንደማይችል ያለፉት ሃያ ዓመታት በቂ ማሳያ ነው፡፡ ስለሆነም አንድነት በሀገራችን የዜጎች መብት ማስከበር ጉዳይን ማዕከላዊ ስፍራ እንዲይዝ ይታገላል፡፡ በሌላ በኩል በብሔረሰብ ዙሪያ መደራጀት ዴሞክራሲያዊ መብት እንደሆነ አንድነት ይቀበላል፡፡ ይሁን እንጂ በብሔረሰብ ዙሪያ የተደራጁ ወገኖች፣ ከዘረኝነት መራቅ አለባቸው ብለን እናምናለን፡፡
ያለፉት አገዛዞች የፈጸሙት በጎ ተግባሮች እንደነበራቸው ሁሉ፣ አስከፊ በደሎች ፈጽመዋል፡፡ ከታሪካችን መልካም የነበሩ ሁኔታዎች ወስደን፣ የተፈጸሙ ግፎች እንዳይደገሙ መታገል ይኖርብናል፡፡ አንድነት ፓርቲ የሀገራችን ፖለቲካ ከታሪክ እስረኝነት መላቀቅ አለበት ብለን እናምናለን፡፡ የኔ ሃሳብ ካልሆነ፣ የሌላውን ሃሰብ መጥፋት አለበት የሚል አመለካከት ቦታ እንደይኖረው ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡
ይህ ትውልድ ዘረኝነትንና ጠባብነትን በማንኛውም ቅርጽና ይዘቱ ቢመጣ ሊታገለው ይገባል፡፡ በባህር ዳርም ሆነ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል የሚታየው ድርጊት ሰፊውን ሕዝብ የሚወክል ተግባር እንዳልሆነ አንድነት ይገነዘባል፡፡
አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ
መጋቢት 19 ቀን 2006 ዓ.ም
አዲስ አበባ

ፍኖተ ነፃነት
By ፍኖተ ነፃነት March 28, 2014 10:32