ከመንግሥት መረጃ የማግኘት መብት አለን!

ፍኖተ ነፃነት
By ፍኖተ ነፃነት July 29, 2012 17:46

ከመንግሥት መረጃ የማግኘት መብት አለን!

ሰሞኑን ዝግጅት ክፍላችን የደረሱንን ዜናዎች ዘወትር
እንደምናደርገው ሚዘናዊለማድረግ ወደ መንግስት ከፍተኛ
የስራ ኃላፊ ደውለን ነበረ፡፡ ኃላፊው የሰጡን መልስ
‹‹እናንተን እንደጋዜጣ አልመለከትም፣ደም ለማፋሰስ ነው››
ብለው ስልክ ዘግተውብናል፡፡
ባለን መረጃ ዓለማችን በርካታ እልቂቶችን አስተናግዳለች፡
፡ በአንደኛው ዓለም ጦርነትና በሁለተኛው ዓለም ጦርነት
የተፈጠረውን የዘር ማጥፋት ማስታወስ ይቻላል፡፡ በሩዋንዳና
በቡሩንዲ የተፈፀመው የዘር ማጥፋት ድርጊት ዘግናኝ ነው፡
፡ አንድ ሃይማኖት አንድ ቋንቋ አንድ ዘር በሆነው ሶማሊያ
ለግል ስማቸው፣ ክብራቸውና ጥቅማቸው የቆሙ የጐሳ
መሪዎች በገነቡት መንደርተኛ አስተሳሰብ ዛሬም በሶማሊያ
መቋጫ ያልተበጀለት ዕልቂት እየተፈፀመ ነው፡፡
ደርግ ሥልጣን በያዘበት ማግስት በታወጀው ቀይ ሽብር
አገራችን አንድ ትውልድ አጥታለች፤ ወንጀለኞቹ በህግ
ቢጠየቁም ጠባሳው ዛሬም አልሻረም፡፡ ኢህአዴግ ሥልጣን
ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ እጅግ ዘግናኝ እልቂቶች ተፈጽመዋል፡፡
የበደኖ፣ ወለጋ ባምባሲ፣ ጂማ፣ አርሲ፣ አርባጉጉ፣ አስቦት
ገዳም ባንዲራና ዘንባባ ይዞ መብቱን ለመጠየቅ አደባባይ
በወጣው የአዋሳ ህዝብ ላይ የተፈፀመው ጭፍጨፋ፣
በጋምቤላ አኝዋክ ህዝብ የተፈፀመው የጅምላ ጭፍጨፋ፣
በድሬዳዋ ከተማ ላይ የተፈፀመው የግፍ ግድያ፣ በምርጫ
97 የአዲስ አበባ ህዝብ ቅንጅትን በመምረጡ የተፈፀመ የግፍ
ጭፍጨፋና ግድያን ማስታወስ ይቻላል፡፡ ጨፍጫፊዎቹም
አስጨፍጫፊዎቹም እስከ ዛሬ ለህግ አልቀረቡም፡፡ በአገራችን
ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ደም
እንዲፈስ አንፈልግም፡፡
ደም አፍሳሾች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አምርረን
እንጮሓለን፡፡ “ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል”
እንደሚባለው ኢህአዴግ የራሱን እምነት በኃይል ለመጫን
የሚፈፀመውን ድርጊት ማቆም አለበት ብለን እናምናለን፡
፡ ኢህአዴግ “በሃይማኖት ጉዳይ እጄን አላስገባም” ቢልም
በተጨባጭ ግን እጁን በረጅሙ ዘርግቶ ሃይማኖትን
እያመሰ ነው፡፡ በየቤተክርስቲያኑና በየመስጊዱ ወንጌልና
ቁራን ከሚሰበክ ይልቅ የካድሬዎች ሰበካ አይሎ ይገኛል፡
፡ ኢህአዴግ በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት
ፈጽሞአል፡፡ በልማት ስም በዋልድባ ገዳም እየተፈፀመ
ያለውንም ማንሳት ይቻላል፡፡
ሲኖዶስ ተሰብስቦ በሃይማኖቱ አመራሮችና በእምነቱ ቀኖና
ላይ ሲመክር የኢህአዴግ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ስብሰባው
ላይ እየተቀመጡ ድምጽን በድምፅ እየሻሩ የፈፀሙትንና
እየፈፀሙት ያለውን ድርጊት ተገቢ ነው ብለን አናምንም፡፡
በእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ እየደረሰ ያለው ጣልቃ
ገብነት መቆም አለበት፡፡ ኢህአዴግ የሃይማኖት ሥልጠና
መስጠትም ማስተባበርም አይጠበቅበትም፡፡ የሃይማኖቱ
መሪዎች የሚመረጡት በቀበሌ መስተዳድር ውስጥ ሳይሆን
በየመስጊዳቸው በራሳቸው አጀንዳ ሊሆን ይገባል፡፡ ካድሬና
ደህንነት ሙስሊሙን ህብረተሰብ እየሰበሰበ የሚያጉላላበት
ሂደት መቆም አለበት ብለን እናምናለን፡፡ በአጠቃላይ ኢህአዴግ
ከደም አፋሳሽ ተግባሩ ተቆጥቦ መንግስታዊ ኃላፊነቱን
መወጣት አለበት፡፡ እኛ አንድም ጠብታ ደም እንዳይፈስ
እንፈልጋለን፡፡ እኛ የደም ጥማት የለብንም፡፡ ጥማታችን
ፍትህ፤ ሠላም፣ ፍቅር፣ የህግ የበላይነት፣ የመናገርና
የመጽሐፍ መብት የሆነው ዴሞክራሲያዊ መብቶች
እንዲሁም ሰብአዊ መብቶች ናቸው፡፡ ደም አፍሳሾችም
ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡ ዛሬም
እውነትን እንዘግባለን፡፡ ለሠላም ለህግ የበላይነት እንሰራለን፡
፡ ደም አፍሳሾች ለህግ እንዲቀርቡ እንጮሃለን፡፡
ይህን ሀቅ በመንተራስና በህገ መንግሥቱ ላይ የተደነገጉ
አንቀፆችን ዋቢ በማድረግ ህዝብ ከመንግስት መረጃ የማግኘት
መብት እንዳለው ደጋግመን መግለጽ እንወዳለን፡፡

ፍኖተ ነፃነት
By ፍኖተ ነፃነት July 29, 2012 17:46