በእነአንዷለም መዝገብ 24ቱ ተከሳሾች ተከላከሉ ተባሉ

ፍኖተ ነፃነት
By ፍኖተ ነፃነት January 25, 2012 20:39

ሙሉ ገ./ኢዲስነገር ኦንላይን

ረቡዕ ጥር 16 ቀን 2004 ዓ.ም፡- የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት በሽብርተኝነት ወንጀል “ተጠርጥረዋል” ተብለው በእነአንዷለም አራጌ የክስ መዝገብ በተከሰሱ 24 የተቃዋሚ ፓርቲ የአመራር አባላት፣ ጋዜጠኞች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ላይ  “በተወሰኑት ክሶች ላይ ወንጀሉን ስላለመፈጸማችሁ ተከራክራችሁ አስረዱ” ሲል ዛሬ ከሰአት በኋላ ብይን ሰጠ፡፡ ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን የመከላከያ ምስክር ለማድመጥ ለየካቲት 26 እና 27 ቀን 2004 ዓ.ም ጊዜ ቀጠሮ  ሰጥቷል፡፡

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ (አንድነት) ፓርቲ ምክትል ሊቀ መንበርና የሕዝብ ግንኙነት ሐላፊ አቶ አንዷለም አራጌ “ድሮውንም ፍርድ ቤቱ ነጻ እንዳልሆነ ይታወቃል፤ ፍርዱ ቀደም ብሎ ከቤተ መንግሥት በጠ/ሚ መለስ ዜናዊ እንደተሰጠን የመንግሥት አፍ በሆነው የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ድርጅት ከፍርድ ቤቱ በፊት የወንጀለኝነት ፍርዳችንን ሲያስተጋባ እንደ ነበር ይታወቃል፡፡” በማለት በችሎቱ ተናግሯል። የቀኝ ዳኛ ሙሉጌታ ኪዳኔ በዚህ ተበሳጭተው በኀይለ ቃል ዝም በል ሲሉትም “ፍርድ ቤቱ መብቴን ሊያስከብርልኝ እንጂ ሊያስፈራራኝ አይገባም” በማለት መልስ ሰጥቷል፡፡

የግራ ዳኛ በሪሁ አራጋው “በተለይ 1ኛ ተከሳሽ አቶ አንዷለም አራጌ እና 5ተኛ ተከሳሽ አቶ ክንፈሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ) በችሎት ሐሳባችሁን የመግለጽ መብት አላችሁ ስትባሉ ፍርድ ቤቱን ለማሳጣት የምትጠቀሙት ቃላት ችሎት በመዳፈር የሚያስቀጣ ነው፤ እናንተ ለችሎት ታዳሚውና በሌላ በኩል መልእክት እያስተላለፋችሁ ይሆናል፤ ነገር ግን ይህ የፍርድ ቤት ክብርን መዳፈር ነው፡፡ ድጋሚ እንደዚህ እንዳትናገሩ፡፡ የፍርድ ቤቱን ክብር የሚነኩ የሚዲያ ተቋማት ካሉ እነርሱ ተጠርተው የሚጠየቁበት አሰራር አለ፡፡ እኛ ለቀረቡልን አቤቱታዎች ትዕዛዝ ሰጥተናል፡፡ ይሄ ችሎት የእናንተን ጉዳይ ስለተመለከተ ሁሉንም የእናንተን በደል ማየት ይችላል ማለት አይደለም፡፡ የሚዲያ አሰራር ደንብ አለ፣ የመገናኛ ብዙንና ሐሳብን በነጻ የመግለጽ መብት የሚዳኝበት ሁኔታ አለ፡፡ በተረፈ ቀደም ብሎ ፍርድ ተሰጥቷል ብላችሁ ፍርድ ቤቱን ማንጓጠጥ ሊያስጠይቃችሁ ይችላል፡፡ ከጠበቆቻችሁ ጋር ብትመካከሩ ይሻላል” ብለዋል፡፡

 

5ተኛ ተከሳሽ ክንፈሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ) በበኩሉ “በቀረበብኝ 5ተኛው ክስ ላይ የኤርትራ መንግሥትና የሻቢያ ተላላኪ ሆኗል ይል ነበር፣ ነገር ግን ፍርድ ቤቱ በክሱ ላይ በቂ ማስረጃ ባለመቅረቡ ክሱን ውድቅ አድርጎት እያለ ትላንትና ከትላንት ወዲያ የመንግሥት ሚዲያ የሆነው የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ድርጅት እኔን ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር አያይዞ እያቀረበ ወንጀለኛ እያደረገኝ ስለሆነ ፍርድ ቤቱ ሁኔታውን እንዲገነዘበውና እርምጃ እንዲወስድልኝ እጠይቃለሁ” ብሎ ቅሬታ ቢያቀርብም ፍርድ ቤቱ ግን ውድቅ አድርጎታል፡፡

 

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በችሎቱ ማጠቃለያ ላይ “የቀረበብኝ የሐሰት ክስ ነው ፣ ከግንቦት 7 ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነትና ንክኪ የለኝም፤ ይህንን ሁሉም ሕዝብ እንዲያውቅልኝ እፈልጋለሁ፤ ከተመሰረተብኝ ክስ ነጻ እና ንጹህ ሰው ነኝ” በማለት ተናግሯል፡፡

 

ዛሬ ከሰአት በኋላ ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ላይ በዋለው ሦስተኛ ወንጀል ችሎት የመሐል ዳኛ እንዳሻው አዳነ የፍርድ ቤቱን ብይን በንባብ አሰምተዋል። የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾች ላይ ካቀረባቸው ስድስት ክሶች ውስጥ በ1ኛው ክስ ሁሉም  የተከሰሱ ሲሆን አንዷለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮንን፣ ዮሐንስ ተረፈ፣ ሻምበል የሸዋስ ይሁንአለም፣ ክንፈሚካኤል ደበበ፣ ምትኩ ዳምጤ፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ አንዷለም አያሌው፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ ውቤ ሮቤ፣ መስፍን አማን፣ ዘለሌ ጸጋ ስላሴ፣ ጋዜጠኛ ፋሲል የኔአለም፣ አበበ በለው፣ ኦባንግ ሜቶ የተባሉት ተከሳሾች ወንጀሉን ስላለመፈጸማቸው እንዲከላከሉና እንዲያስረዱ፤ በአንፃሩ በኤፍሬም ማዴቦ፣ አበበ ገላው፣ ንአምን ዘለቀ፣ ኤልያስ ሞላ፣ ደሳለኝ አራጌ ዋለ፣ ኮ/ል አለበል አማረ በተባሉት ተከሳሾች ላይ ግን ዐቃቤ ሕግ ክሱን የሚያስረዳ በቂ ማስረጃ ባለማቅረቡ መከላከል ሳያስፈልጋቸው ነጻ ወጥተዋል ብሏል- ፍርድ ቤቱ፡፡  ክሱ በጸረ ሽብር ሕጉን አንቀጽ 3/1-4፣ አንቀጽ 4 እና 6 የተደነገገውን በመተላለፍ በሚል የቀረበ ነው። በክስ ቻርጁ ሁሉም ተጠርጣሪዎች በዚህ ክስ ቢካተቱም በኋላ ዐቃቤ ሕግ 23ኛ እና 24ኛ ተከሳሾች “በታይፕ ስሕተት” መግባታቸውን በመጥቀስ ከዝርዝሩ ወጥተዋል። የክሱ ጭብጥ በጥቅሉ የሽብር ድርጊት መፈጸም ወይም ለዚሁ መዘጋጀትንና ማሴርን፣ እንዲሁም ሽብርተኝነትን ማበረታታን የሚመለከት ነው።

 

2ተኛው ክስ የቀረበባቸው ከተከሳሽ ተራ ቁጥር 1 እስከ 18ተኛ ተራ ቁጥር ድረስ ያሉት ሲሆኑ 9ነኛ፣ 10ኛ፣ 11ኛ፣ 12ኛ፣ 16ኛ፣ 17ኛ፣ 18ኛ ተከሳሾች የቀረበባቸውን ክስ እንዲከላከሉ ብይን የሰጠው ፍርድ ቤት በአንፃሩ 1ኛ፣ 3ተኛ፣ 4ተኛ እና 5ተኛ ተከሳሾች መከላከል ሳያስፈልጋቸው ከ2ተኛው ክሱ ነጻ ናቸው ብሏል፡፡ 2ኛ ክስ የወንጀል ሕጉን አንቀጽ 32 (1-ሀ) እና አንቀጽ 38 (1)፣ እንዲሁም የጸረ ሽብር ሕጉን አንቀጽ 7 (2) በመተላለፍ የቀረበ ነው። የክሱ ጭብጥ በጥቅሉ በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ በአመራርነት መሳተፍን የሚመለከት ነው።

 

4ተኛ ክስ በሁሉም ተከሳሾች ላይ የቀረበ ሲሆን ሁሉም እንዲከላከሉ ፍርድ ቤቱ ብይን መስጠቱን አስታውቋል፡፡ ክስ፤ የወንጀል ሕጉን አንቀጽ 32 (1-ሀ) እና አንቀጽ 248 (ለ) የሚደነግገውን በመተላለፍ በሚል የተመሠረተ ነው። የክሱ ጭብጥ የአገር ክህደት እና ለጠላት አገር እርዳታ መስጠትን ይመለከታል።

 

በአንጻሩ በ3ተኛ እና በ5ተኛ ክሶች ላይ ግን ዐቃቤ ሕግ በቂ መረጃ ሊያቀርብ ባለመቻሉ ተከሳሾች መከላከል ሳያስፈልጋቸው ከክሱ ነጻ ወጥተዋል ሲል ፍርድ ቤቱ ወስኗል። 5ኛው ክስ፤ የወንጀል ሕጉን አንቀጽ 32 (1-ሀ)፣ አንቀጽ 38 (1/ሀ)  እና 252 (1) በመተላለፍ የተመሠረተ ነበር። የክሱ ጭብጥ በጥቅሉ ለጠላት አገር መሰለልን የሚመለከት ነው። ሦስተኛው ክስ ደግሞ ከሽብርተኛ ድርጅት ሰዎችን መመልመልን የሚመለከት ነበር።

 

በ6ተኛው ክስ ላይ ከሀገር ውጪ የሚገኙት ተከሳሾች እንዲከላከሉ ሲል ብይን አስተላልፏል፡፡ክሱ የወንጀል ሕጉን አንቀጽ 32 (1-ሀ) እና አንቀጽ 38 (6)፣ እንዲሁም የጸረ ሽብር ሕጉን አንቀጽ 5 (1) በመተላለፍ ሽብርተኝነትን እና ሽብርተኛ ድርጅቶችን ማበረታታትን የሚመለከት ነው።

 

24ቱ ተከሳሾች የሚከቱሉት ናቸው።

 1. አንዷለም አራጌ
 2. ናትናኤል መኮንን
 3. ዮሐንስ ተረፈ
 4. የሺዋስ ይሁንዓለም (ሻምበል)
 5. ክንፈሚካኤል ደበበ
 6. ምትኩ ዳምጤ
 7. እስክንድር ነጋ
 8. አንዷለም አያሌው
 9. አንዳርጋቸው ጽጌ
 10. ብርሃኑ ነጋ (ዶ/ር)
 11. ውቤ ሮቢ
 12. ኤርሬም ማዴቦ
 13. መስፍን አማን
 14. ዘለሌ ጸጋሥላሴ
 15. ፋሲል የኔዓለም
 16. አበበ በለው
 17. አበበ ገላው
 18. ንአምን ዘለቀ
 19. ኤልያስ ሞላ
 20. ደሳለኝ አራጌ
 21. አለበል አማረ (ኮሎኔል)
 22. ኦባንግ ሜቶ
 23. መስፍን ነጋሽ
 24. ዐቢይ ተ/ማርያም

 

 

ፍኖተ ነፃነት
By ፍኖተ ነፃነት January 25, 2012 20:39